የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የተመሰረተበትን 23ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ ከኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

 

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት 23ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት ከኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

የኦሮሞ ሕዝብን የዘመናት ትግል ትክክለኛ ፈር አስይዞ በመምራት የትጥቅ ትግሉ ምዕራፍ በድል ተደምድሞ የህዝቡ መብትና ክብር የተረጋገጠበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እውን እንዲሆን ወደር የሌለው መስዋዕትነት የከፈለውና ሕዝቡ በተፈጠረለት ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ በእድገት ጎዳና ላይ በድል እየተራመደ ዛሬ ለሚገኝበት ደማቅ ታሪካዊ ወቅት ላይ እንዲደርስ መተክያ የሌለው የአመራር ሚና የተጫወተው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ የተመሰረተበት በዓል ዘንድሮ ለ23ኛ ጊዜ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡ ከ23 ዓመት በፊት መጋቢት 17 ቀን ኦህዴድን በመመስረት የተሰራው ታላቅ ክንውን በኦሮሞ ሕዝብ የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ የጠራ መሰመር ያለው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ድርጅት ዕውን የሆነበትና በሕዝብ የዘመናት ትግል ውስጥ ተከስቶ የነበረው የሀቀኛ መሪ ደርጅት እጦት ችግር የተወገደበት፣ የኦሮሞን ሕዝብ ከወንድሞቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በመነጠል በኦሮሞ ነፃነት ስም ለአዲስ የጭቆና አገዛዝ ለመዳረግ የተሸረበው ሴራ የከሸፈበትና የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች የአትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ክንዱን አስተባብሮ  በልጆቿ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለምትገነባ አዲስቷ ኢትዮጵያ ዕውን መሆን ድርሻውን እንዲወጣ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ታሪካዊ ክንውን ነው፡፡
በመሆኑም ኦህዴድ የተመሠረተበት  ዕለት በኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ ያለው የድል በዓል ነው፡፡ በተለይም በዓሉ ለድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣ እንደዚሁም ለመላ የኦሮሞ ሕዝብና  በክልሉ ለሚገኙ የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች አባላት ያለው ትርጉም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ድርጅታችን ኦህዴድ የተመሰረተበት ቀን የኦሮሚያ ክልል ሕዝብና የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች በድርጅታችን አመራር የተጀመረውን የጸረ-ድህነት ትግል አጠናክሮ ለመቀጠልና አገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ቃል ኪዳናቸውን የሚያድሱበት መልካም አጋጣሚ በመሆን ሲከበር ቆይቷል፡፡ የዘንድሮው 23ኛው የኦህዴድ የምስረታ በዓል የሚከበረው ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ የበሳልና  ጠንካራ ድርጅታዊ አመራር ባለቤት ሆና በአዲስ መሰረት ላይ እንደትዋቀርና ትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫን ተከትላ በህዳሴ ጎዳና ላይ በድል እንድትረማመድ ወደር የሌለው የአመራር ሚና የተጫወቱት ውዱ ሊቀመንበራችን ጓድ መለስ ዜናዊ በተሰውበትና ራዕያቸውን ለማሳካት ድርጅታችንና ሕዝባችን ጠንክረው እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት ላይ በመሆኑ በዓይነቱ ልዩና ታሪካዊነቱ እጅግ የጎላ ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር የዘንድሮው የኦህዴድ የምስረታ በዓል የድርጅታችን ኦህዴድና የኢህአዴግ ጉባኤዎች በተካሄዱ ማግስት የሚከበር መሆኑ በዓሉን የበለጠ  ድምቀት አላብሶታል፡፡ ስለሆነም ድርጅታችን ኦህዴድ ይህንን ታላቅና ታሪካዊ በዓል ሲያከብር ክልላዊና አገራዊ የአመራር ሚናውን ይበልጥ በማሳደግ በተደራጀ የሕዝብ ተሳትፎ የድርጅታችንን ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በብቃት ስራ ላይ በማዋል የመለስ/ኢህአዴግን ራዕይ ለማሳካት ከመቼውም በላቀ ቁርጠኝነት መንቀሳቀሱን እንደሚቀጥል ቃል ኪዳኑን ያድሳል፡፡
ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ
መላ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች
ድርጅታችን ኦህዴድ/ኢሕአዴግ የኦሮሞ ሕዝብና ባጠቃላይም የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በኃይል የተጫነባቸውን የጭቆና ቀንበር አሽቀንጥረው እንዲጥሉና መብትና ነፃነታቸውን እንዲያስከብሩ የበኩሉን ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደከፈለ ሁሉ ዛሬም በአገር ግንባታው ትግል ግንባር ቀደም የአመራር ሚናውን በአስተማማኝ ብቃት በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ በድርጅታችን ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ አመራር ትክክለኛና ውጤታማ የልማት ስትራተጂዎችንና አቅጣጫዎችን ይዘን በድህነትና በኃላቀርነት ላይ የጀመርነው ጦርነት በማያባራ ሁኔታ ተፋፍሞ ቀጥሏል፡፡  በዚህም ሂደት የድርጅታችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በሕዝባችን ውስጥ እየሰረፁ በመሄዳቸው በሰፊ ሕዝባዊ  ተሳትፎ የታጀበ የፀረ- ድህነት እንቅስቃሴን ለመፍጠርና በሁሉም መስክ አመርቂ የልማት ውጤቶች መመዝገብ የጀመሩበትን ብሩህ የታሪክ ምዕራፍ ለመክፈት በቅተናል፡፡
በመሆኑም ባለፉት ዓመታት ኦህዴድና በእሱ የሚመራው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉን አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈንና የፈጣን ልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አላማዎቻችንን ከግብ ለማድረስ መላውን የክልሉን ሕዝብ በማስተባበር ቀጣይነት ባለው መልክ ባካሄዱት እንቅስቃሴ ክልላችን በታላቅ የለውጥና የዕድገት ጎደና ላይ መገኘቱን በግልፅ ያመላከቱ እጅግ መሰረታዊ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ችለናል፡፡ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ይህንን አመርቂ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና ለአገራችን የህዳሴ ጉዞ ክልላችን ድርሻውን በብቃት እንዲወጣ ለማስቻል የተለጠጡ የልማት ግቦችን ይዘን እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት በከፍተኛ ርብርብ ላይ እንገኛለን፡፡
በዚህ ረገድ የአምስት አመቱን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በአገር አቀፍ ደረጃና በክልላችን በኦሮሚያ ውስጥ በሚገባ ስራ ላይ ለማዋል በድርጅታችን ኦህዴድ/ኢሕአዴግ አመራር የተያያዝናቸው ሰፋፊ ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የአምስት አመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቦች የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ ከማፋጠን አኳያ ልዩ ትርጉም ያላቸው መሆናቸውን በመገንዘብ የድርጅታችን አባላትና፣ ደጋፊዎች በአጠቃላይም መላ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ለተፈፃሚነቱ እያሳዩ ያሉት ተነሳሽነት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ ድርጅታችን ኦህዴድም በሁሉም የኢኮኖሚና ማህበራዊ የልማት መስኮች የተያዙ እቅዶች በአግባቡ እንዲፈጸሙና የታሰበው ውጤት እንዲመዘገብ ግንባር ቀደም ሆኖ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
በዚሁ መሰረት በድርጅታችን አመራርና በተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ በሁሉም የልማት ዘርፎች የቀጣይ ጉዞአችንን ብሩህነት ከወዲሁ ያረጋገጡ ውጤቶች እየተመዘገቡ መጥተዋል፡፡
 በዚህ ረገድ ድርጅታችን ባለፉት ሁለት ዓመታት መላ የአመራር አባላቱን አቅም ቀጣይነት ባለው ስልጠና በማሳደግና፣ የክትትልና የድጋፍ ስራን በማጠናከር ያደረገው መረባረብ ለአመራሩ ጥንካሬና በየመስኩ ለተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ 23ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው እነዚህን ውጤታማ የለውጥና የዕድገት ስራዎች ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና የህዳሴ ጉዞውን ይበልጥ ለማፋጠን ያለውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ነው፡፡ ኦሕዴድ ራሱን በየጊዜው እየገመገመ ከጥንካሬውና ከድክመቱ የመማርና ስህተቱን እያረመ በማያቋርጥ ሁኔታ ራሱን እያጠናከረ የመሄድ ባህል ያዳበረ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንደመሆኑ ይህንን በዓል ሲያከብር አጠቃላይ ዝግጁነቱንና ብቃቱን ይበልጥ እየሳደገ የተጀመሩትን የልማት ስራዎች ከግብ ለማድረስ የሚጠበቅበትን የአመራር ድርሻ በላቀ ብቃት ለመውጣት ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል፡፡
ይህንንም ዕውን ለማድረግ በየደረጃው ያለውን አመራርና የመላ አባላቱን ፓለቲካዊና ድርጅታዊ አመራር ብቃት ይበልጥ ለማሳደግና በሁሉም አካላት ውስጥ ጠንካራ የማስፈፀም አቅም ለመገንባት ሲያደርግ የቆየውንና ውጤታማ እየሆነ የመጣውን የአመራር ስልጠናና የሪፎርም ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
እንደሚታወቀው ድርጅታችን የተመሰረተበት 23ኛ ዓመት በዓላችን እየተከበረ ያለው የአከባቢና የከተማ አስተዳደር ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅቱ በተጠናቀቀበት ወቅት ላይ ነው፡፡ በቀጣዩ ሚያዝያ ወር የሚካሄደው ይህ ምርጫ በየደረጃው ያለውን ሕዝባዊ አስተዳደር ይበልጥ ለማጠናከርና የማስፈፀም አቅማቸውን ከመቸውም በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግ ድርጅታችን ኦህዲድ ላቀዳቸው ስራዎች መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው፡፡  በዚሁ መሰረት ኦህዴድ በየደረጃው ይመጥናሉ ብሎ ያመነባቸውንና በሕዝብ አስገምግሞ ይሁንታ ያገኘባቸውን ዕጩዎች ለምርጫ አቅርቧል፡፡ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና  ፍትሃዊ  ሆኖ የሕዝቡን አመኔታ ባረጋገጠ መልኩ እንዲጠናቀቅም ኦሕዴድ የበኩሉን ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በክልላችን ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የጋራ መድረክ ፈጥሮ ለምርጫው ስኬት ግንባር ቀደም ሆኖ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ሕዝባችን በዘንድሮው ምርጫ ለመሳተፍ በነቂስ ወጥቶ እንደተመዘገበ ሁሉ በምርጫው ዕለትም ካርዱን ተጠቅሞ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመራችንን በመምረጥ የሕዝቦችን መብት ላስከበረውና ፈጣን ዕድገትን ላረጋገጠው ሥርዓታችን መጠናከር የተለመደ ድጋፉን እንዲቀጥል  የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በዚህም አጋጣሚ መላ የኦሮሞ ሕዝብና የክልላችን የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች አባላት በኦህዴድ አመራር በዕድገት ጎዳና ላይ በድል እየተራመዱ ለዚህ  ብሩህ ወቅት መድረስ እንደቻሉ ሁሉ በቀጣይም ለህዳሴ ጉዞአችን ስኬት የኦሕዴድ/ ኢሕአዴግ አመራር ወሳኝ መሆኑን ተገንዝበው ከድርጅታችን ጋር ሆነው የጀመሩትን ውጤታማ የልማት እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስና የታላቁ መሪያችንን ራዕይ ለማሳካት የልማት ሰራዊት አደረጃጀታችውን አጠናክረው ከመቸውም በላቀ ቁርጠኝነት እንዲረባረቡ ኦህዴድ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
መላ የኦህዴድ አባላትና ደጋፊዎችም የታላቁ መሪያችንን የፅናት ተምሳሌት ተላብሰው በዚህ ወሳኝ የዕድገት እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ደርጅታችን ኦህዴድ ያለውን እምነት እየገለፀ መጪው ወቅት በሁሉም መስክ ተጨማሪ ድሎችን የምናስመዘግብበት የስኬትና የደስታ ወቅት እንዲሆን ያለውን ልባዊ ምኞት ይገልፃል፡፡
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ
መጋቢት 19 ቀን 2005 ዓ.ም
ፊንፊኔ